እስልምና እና ሽብርተኝነት
ማርክ ኤ. ገብርኤል
ቅንብር በአዘጋጁ

ምዕራፍ ሦስት
አንድ ዓመት ያለምንም እምነት



ቀጣዩን ሳምንት በደቡባዊ ካይሮ በሚገኝ ወኅኒ ቤት ውስጥ አሳለፍኩኝ፡፡ በንፅፅር የተሻለ ነፃነት ያለው ጊዜ ነበር፡፡ ከአክራሪ እስልምና ጋር የማይስማማ የእስረኞች ጠባቂ እግዚአብሔር ላከልኝ፡፡


በዚህ ሁሉ ጊዜ ቤተ ሰቦቼ ያለሁበትን ለማወቅ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በግብፅ ፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበረው የእናቴ ወንድም ከባሕር ማዶ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ግን አልተሳካላቸውም ነበር፡፡ እናቴ እያለቀሰች ደውላ እንዲህ አለችው፡ “ለሁለት ሳምንታት ያህል ልጃችን ያለበትን አናውቅም፣ ተለይቶናል፡፡” አጎቴ አስፈላጊ የሆኑት ግንኙነቶች ሁሉ ነበሩት፡፡ እኔ ከተጠለፍኩኝ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ይፈታ የሚል የትዕዛዝ ወረቀት ይዞ በመምጣት ወደ ቤት ይዞኝ ሄደ፡፡


በኋላም ፖሊስ ለአባቴ የሚከተለውን ሪፖርት ሰጠ፡

ልጅህ እስልምናን መልቀቁን የሚገልፅ የፋክስ መልዕክት ከአል-አዝሃር ደርሶን ነበር፡፡ ነገር ግን ከአስራ አምስት ቀናት ምርመራ በኋላ ይህንን የሚደግፍ ምንም ማስረጃ አላገኘንም፡፡

አባቴ ይህንን በመስማቱ እፎይታ ተሰማው፡፡ ከወንድሞቼ እና እህቶቼ መካከል በዩኒቨርሲቲ እስልምናን ያጠናሁት እኔ ብቻ ስሆን እርሱም በእኔ ይኮራ ነበር፡፡ እኔ እስልምናን እንደምለቅ በፍፁም አስቦ ስለማያውቅ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉት ሰዎች ስለ እኔ ምሑርነት መጥፎ አመለካከት እንዳላቸው በማሰብ ሁኔታውን ሁሉ ከዝያ ጋር አያያዘ፡፡


“እኛ አንፈልጋቸውም” በማለት በእርሱ ፋብሪካ ውስጥ የሽያጭ ኃላፊ ሆኜ ወዲያውኑ ሥራ እንድጀምር ጠየቀኝ፡፡ የቆዳ ጃኬቶች እና የወንዶችን እንዲሁም የሴቶችን ልብስ የሚያመርት የተሳካለት ንግድ ነበረው፡፡


አንድ ዓመት ያለ እምነት


ለአንድ ዓመት ምንም እምነት ሳይኖረኝ ኖርኩኝ፡፡ ወደ እርሱ የምፀልየው፣ የምጠራው ወይንም የምኖርለት አምላክ አልነበረኝም፡፡ ቸር እና ፃድቅ የሆነ አምላክ መኖሩን አውቃለሁ ነገር ግን እርሱ ማን እንደሆነ አላውቅም ነበር፡፡ እርሱ የሙስሊሞች፣ የክርስቲያኖች ወይንም ደግሞ የአይሁዶች አምላክ ነውን? እንደ ህንዶች ላም ዓይነት የሆነ እንስሳ ነውን? እንዴት ላገኘው እንደምችል ምንም የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡


አንድ ሙስሊም እስልምና እውነት ዓይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚቀየርበትን ሌላ ኃይማኖት ካላገኘ በሕይወቱ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪው ጊዜ እንደሚሆንበት መረዳት አለባችሁ፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ሰው እምነት ሥጋና ደም ውስጥ የሰረፀ ነገር ነው፡፡ አምላኩን ሳያውቅ መኖር አይታየውም፡፡


ዓመቱን በሙሉ በመንፈሴ ውስጥ የነበረውን ህመም ውጫዊው አካሌ ይገልጠው ነበር፡፡ የሚያስፈልገኝ ቁሳዊ ነገር ሁሉ ቢኖረኝም የእውነተኛውን አምላክ ማንነት ለማወቅ ያለ እረፍት አስብ ስለነበር አካሌ በድካም እጅግ ደክሞ ነበር፡፡ በማያቋርጥ የራስ ምታት እሰቃይ ነበር፡፡ ዘመዳችን ወደነበረ አንድ ዶክተር ዘንድ ሄጄ ነበር፡፡ አዕምሮዬን ቢመረምረኝም ነገር ግን ምንም ችግር ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ሊረዱኝ የሚችሉ የተወሰኑ የሚዋጡ መድኃኒቶችን አዘዘልኝ፡፡


የተራራው ስብከት


የራስ ምታቱ ቶሎ እንደሚለቀኝ ስላሰብኩኝ አነስተኛ መጠን ያላቸውን መድኃኒቶች ለመግዛት በሳምንት አንድ ጊዜ ወይንም ሁለት ጊዜ በቅርበት ወዳለ የመድኃኒት መደብር መሄድ ጀመርኩኝ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ከተመላለስኩኝ በኋላ ፋርማሲስቷ “በሕይወትህ ውስጥ ምን እየሆነ ነው?” በማለት ጠየቀችኝ፡፡


“ምንም ነገር እየሆነ አይደለም፡፡ ችግሬ አንድ ነገር ብቻ ነው፡ ያለ አምላክ እየኖርኩኝ ነው፡፡ አምላኬ ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔንም ሆነ አፅናፈ ዓለሙን የፈጠረው ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡” በማለት መለስኩላት፡፡


እርሷም “ነገር ግን እኮ አንተ በጣም በተከበረ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ነበርክ፡፡ ቤተሰብህም በህብረተሰቡ ውስጥ በጣም የተከበረ ነው፡፡” በማለት መለሰችልኝ፡፡


“ልክ ነሽ እርሱስ እውነት ነው” በማለት መለስኩላት፡፡ አልኳትም፡ “ነገር ግን በአስተምህሯቸው ውስጥ ውሸትን አገኘሁበት፡፡ ቤቴና ቤተሰቦቼ በእውነት መሰረት ላይ እንደተመሰረቱ ከእንግዲህ በኋላ ማሰብ አልችልም፡፡ ዘወትር በእስልምና ውሸቶች ውስጥ ተጀቡኜ እኖር ነበር፡፡ አሁን ግን እርቃኔን እንደቀረሁኝ ይሰማኛል፡፡ በልቤ ውስጥ ያለውን ባዶነት እንዴት አድርጌ ነው መሙላት የምችለው? እባክሽኝ እርጂኝ፡፡”


“እሺ፣ ዛሬ እነዚህን ክኒኖች እና ይህንን መጽሐፍ - መጽሐፍ ቅዱስን እሰጥሃለሁ፡፡ ከዚህ መጽሐፍ የሆነ ነገር ከማንበብህ በፊት ምንም መድኃኒት እንደማትውጥ እባክህን ቃል ግባልኝ” አለችኝ፡፡


መጽሐፉን ወደ ቤቴ በመውሰድ በአቦ ሰጡኝ ዝም ብዬ አንድ ቦታ ላይ ከፈትኩኝ፡፡ ዓይኖቼ ማቴዎስ 5፡38 ላይ አረፉ፡


“ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት።”


ሰውነቴ በሙሉ መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ ቁርአንን እድሜዬን በሙሉ ሳጠናው ነበር ነገር ግን እንደዚህ የሚያነቁ ቃላትን አንድም እንኳ አግኝቼ አላውቅም፡፡ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ፊት ለፊት ተገናኘሁ፡፡


ከጊዜ መዘውር ውጪ ሆንኩኝ፡፡ በኮረብታ በላይ ባለ ደመና ላይ ተቀምጬ ከፊት ለፊቴ ደግሞ የአፅናፈ ዓለም ትልቁ መምህር ከፊት ለፊቴ በመሆን ስለ ሰማይ ሚስጥር እና ስለ እግዚአህሔር ልብ እየነገረኝ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡


መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ለዓመታት ካጠናሁት ከቁርአን ጋር ማነፃፀር እችል ስለነበር እውነተኛውን አምላክ እንደተገናኘሁት ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ በቀጣዩ ቀን የመጀመርያ ሰዓታት ላይ አሁንም ድረስ ሳነብ ነበር፤ አመሻሽ አካባቢ ላይም ልቤን ለኢየሱስ ሰጠሁኝ፡፡


ሽምቅ

ኢየሱስን መቀበሌን ለፋርማሲስቷ እና ለባለቤቷ ብቻ ነበር የተናገርኩት ነገር ግን በግብፅ አንድ ሰው እስልምናን ከተወ ክርስቲያን እንደሆነ ስለሚታሰብ መገደል አለበት ይባላል፡፡ በዚህ ምክንያት አክራሪዎች ሸምቀው እንዲጠብቁኝ እና እንዲገድሉኝ ሁለት ሰዎችን ልከውብኝ ነበር፡፡


ይህም የሆነው ጓደኛዬ ጋር ቆይቼ ወደ ቤቴ ስመለስ ነበር፡፡ በጊዛ ውስጥ የአስራ አምስት ወይንም የሃያ ደቂቃ የእግር መንገድ ቢሆን ነበር፡፡ ቲርሳኤ ጎዳና በሚባለው ላይ ቤቴ አካባቢ ስደርስ ነበር ሁለት ሰዎችን የግሮሰሪ በር ላይ ቆመው ያየሁት፡፡ ባህላዊ የሆኑትን ረጃጅም ነጫጭ ቀሚሶችን ለብሰው ነበር፤ ጢማቸውም የረዘመ እና በራሶቻቸው ላይም ጠምጥመው ነበር፡፡ ገበያተኞች ብቻ እንደሆኑ አስቤ ነበር፡፡ የሆነ ነገር ያደርጉብኛል ብዬ አልጠረጠርኩኝም ነበር፡፡


ሱቁ ጋር ስደርስ አስቁመውኝ ድንገት ቢለዋዎችን በመምዘዝ እኔን ለመውጋት መሰንዘር ጀመሩ፡፡ ምንም መሳርያ አልያዝኩኝም ነበር፤ ቀኑም ሞቃት ስለነበር ቲ-ሸርት እና ቁምጣ ብቻ ነበር የለበስኩት፡፡ በእጄም ራሴን መከላከል ጀመርኩኝ፡፡ ቢለዋዎቹ በተደጋጋሚ እኔ ላይ በማረፍ ደረቴን ቆራረጡኝ፡፡


ሌሎች ሰዎች በመንገድ ላይ ነበሩ ነገር ግን የረዳኝ አልነበረም፡፡ ተሰብስበው ብቻ ይመለከቱ ነበር፡፡ በነዚያ ዘመናት ይህ የተለመደ ነበር፡፡ የእጅ ድብድብ ቢሆን ኖሮ ሰዎች ጣልቃ ይገቡ ነበር ነገር ግን በቢላዋ ሲሆን ማንም አይጠጋም፡፡ አንድ ሰው ሽጉጥ ቢመዝ ደግሞ ከፊት መሆን አይፈልጉም፡፡


የመመርያው ጥቃት ፈፃሚ ልቤን ለመውጋት ነበር ሲሞክር የነበረው፡፡ አንድ ጊዜ ሊወጋኝ ምንም አልቀረውም ነበር ነገር ግን ዘወር በማለት ተረፍኩኝ፡፡ በአምስት ኢንች ያህል ስቶ ትከሻዬን አገኘኝ፡፡ ቢለዋውን መዞ ሲያወጣ ወደ ታች ተመልክቼ ያየሁትን የደም ፈሳሽ አስታውሳለሁኝ፡፡


መሬት ላይ ወድቄ እንደ ኳስ ትንሽ እየተንከባለልኩኝ ራሴን ለመከላከል ስጥር ነበር፡፡ ከዚያም ሌላኛው ጥቃት ፈፃሚ ሆዴ ላይ ሊወጋኝ ሞከረ ነገር ግን ስለቱ ቦታውን ስቶ የፊት ጭኔ ላይ ወጋኝ፡፡


በዚህ ጊዜ ብዙ ደም ስለፈሰሰኝ ራሴን ሳትኩኝ፡፡ ሁለት ፖሊሶች በሞተር ሳይክል ደርሰው አጥቂዎቼ ሮጠው እስኪሸሹ ድረስ ምንም ተስፋ አልነበረኝም፡፡


ወደ ሆስፒታል ተወስጄ እርዳታ ተደረገልኝ፡፡ ሆስፒታል እያለሁም ለምን ጥቃት እንደተፈፀመብኝ ፖሊስ ጠይቆኝ እንደማላውቅ ተናገርኩኝ፡፡


አሁንም አባቴ እኔ እስልናን መተዌን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን መካዱን ቀጥሏል፡፡ ይህንን ማሰብ እጅግ ተስኖት ነበር፡፡


አባቴ እውነቱን አወቀ


ለአባቴ መስራቴን ቀጥያለሁኝ፤ ስለ አዲሱ እምነቴም መናገር አልፈለኩም ነበር፡፡ በእርግጥ በ1994 ዓ.ም. የንግድ እድሎችን እንድቃኝለት ወደ ደቡብ አፍሪካ ልኮኝ ነበር፡፡ እዚያም ሳለሁኝ ከህንድ ከመጣ ክርስቲያን ቤተሰብ ጋር ሦስት ቀናትን አሳልፌ ነበር፡፡ ስንለያይም ትንሽዬ መስቀል ያለውን የአንገት ሀብል ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ይህች ትንሽ መስቀል በሕይወቴ የአቅጣጫ ለውጥ ምልክት ሆነች፡፡


ከአንድ ሳምንት ትንሽ ካለፈ በኋላ አባቴ በአንገቴ ላይ ያለውን ሀብል አስተዋለ፡፡ በእስልምና ደግሞ በአንገታቸው ላይ ጌጥ ማድረግ የሚችሉት ሴቶች ብቻ ስለሆኑ በጣም ተናደደ፡፡ “ለምንድነው ይህንን ሰንሰለት ያደረከው?” በማለትም ጠየቀኝ፡፡


ምላሴ የሚከተሉትን ቃላት በራሱ ጊዜ የተናገረ ይመስል ነበር፡ “አባዬ ይህ ሰንሰለት አይደለም፡፡ ይህ መስቀል ነው፡፡ ለእኔ፣ ላንተና ለሁሉም ሰው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በመስቀል ላይ የሞተውን ኢየሱስን ይወክላል፡፡ ኢየሱስን እንደ አዳኜ እና ጌታዬ አድርጌ ተቀብየዋለሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችሁ ትቀበሉት ዘንድ ላንተም ሆነ ለተቀሩት ቤተ ሰቦቼ እፀልያለሁኝ፡፡”


መጀመርያ አባቴ እዚያው እመንገድ ላይ ራሱን ሳተ፡፡ የተወሰኑት ወንድሞቼ በፍጥነት የደረሱለት ሲሆን እናቴ በፍርሃት ታለቅስ ነበር፡፡ የአባቴን ፊት በውሃ ሲያጥቡት ሳሉ እዚያው አብሬያቸው ነበርኩኝ፡፡ ሲነቃም አምርሮ ተቆጥቶ ስለነበር መናገር እንኳ ተስኖት ነበር ነገር ግን ዝም ብሎ ወደ እኔ ጣቱን ቀስሮ ያመለክት ነበር፡፡ በታላቅ ቁጣ በተሞላ ድምፅ “ልጃችሁ ኃይማኖቱን ለውጧል፡፡ ዛሬ እርሱን መግደል አለብኝ!” በማለት ጮኸ፡፡


አባቴ በሚሄድበት ቦታ ሁሉ በቆዳ የተሸፈነ ሽጉጥ በብብቱ ስር ይዞ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ (በግብፅ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ባለጠጎች ሽጉጥ ይይዛሉ፡፡) ሽጉጡን በማውጣ ወደ እኔ አነጣጠረብኝ፡፡ መንገዱን ይዤ ወደ ታች መሮጥ ጀመርኩኝ፡፡ ጥግ ይዤም ሳለሁ ጥይቶች እያፏጩ በላዬ በአናቴ ላይ ሲያልፉ እሰማ ነበር፡፡ ሕይወቴን ለማትረፍ መሮጤን ቀጠልኩኝ፡፡

ቤቴን እስከወዲያኛው ለቀቅሁኝ


በግማሽ ማይል ርቀት ወደሚገኘው የእህቴ ቤት ሮጬ ሄድኩኝ፡፡ በአባቴ ቤት የሚገኙትን ልብሶቼን፣ ፓስፖርቴን እና ሌሎች ዶክመንቶቼን በማምጣት እንድትተባበረኝ ጠየቅኋት፡፡ የተፈጠረውን ነገር ማወቅ ስለፈለገች ጠየቀችኝ፤ እኔም “አባዬ ሊገድለኝ ይፈልጋል” በማለት ነገርኳት፡፡ ለምን እንደሆነም ጠየቀችኝ፤ እኔም “አላውቅም፡፡ እርሱን አባዬን ጠይቂው” በማለት መለስኩላት፡፡


ስሮጥ ሳለሁ ወዴት እንደሆነ አባቴ በትክክል አውቆ ነበር ምክንያቱም እኔና እህቴ እንቀራረብ ነበር፤ ቤቷም ደግሞ ቅርብ ነበርና፡፡  አባቴ ወደ እህቴ ቤት መጣ፤ እኔና እህቴም ስንነጋገር ደረሰ፡፡ እምባው በፊቱ ላይ እየፈሰሰ በሩን መደብደብ ጀመረ፤ እንዲህም ይል ነበር፡ “ልጄ እባክሽን በሩን ክፈቺ፡፡” ከዚያም እንዲህ እያለ ጩኸ፡ “ወንድምሽ ሃይማኖቱን ቀይሯል! እስልምናን ትቷል፡፡ አሁኑኑ እርሱን መግደል አለብኝ!”


እህቴ በሩን በመክፈት ልታረጋጋው ሞከረች፡፡ “አባዬ እዚህ የለም፡፡ ምናልባትም ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምን ወደ ቤት ሄደህ አታርፍም፤ ከዚያም እንደ ቤተሰብ ስለዚህ ጉዳይ ልናወራ እንችላለን፡፡”


እህቴ ራርታልኝ ከወላጆቼ ቤት እቃዎቼን ሰብስባ አመጣችልኝ፡፡ እርሷና እናቴ የተወሰነ ገንዘብ ስለሰጡኝ ነሐሴ 28/1994 አመሻሽ ላይ መኪናዬ ውስጥ ገብቼ እየነዳሁ ሄድኩኝ፡፡


ለሦስት ወራት ያህል በሰሜናዊ ግብፅ፣ ሊብያ፣ ቻድ እና ካሜሩን ለመጓዝ ስታገል ነበር፡፡ በመጨረሻም ኮንጎ ላይ ቆም አልኩኝ፡፡ በዚያን ጊዜ ወባ ይዞኝ ነበር፡፡ እንዲመረምረኝ ግብፃዊ ዶክተር አገኙ፡፡ እኔም ጠዋት ላይ እንደሚሞት ስለተናገረ በኮንጎ ከሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ የሬሳ ሳጥን ለማግኘት እና ወደ ሃገር ቤትም ሊልኩኝ ሁኔታዎችን አመቻቹ፡፡


ለእነርሱ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በበነጋው ነቃሁኝ፡፡ ከአምስት ቀናት በኋላ ሆስፒታሉን ለቅቄ በመውጣት በሁሉም ቦታ ኢየሱስ ያደረገልኝን ለሰዎች መንገር ጀመርኩኝ፡፡


ሕይወት እንደ ኢየሱስ ተከታይ


ኢየሱስን እንደ ግል አዳኜ አድርጌ ከተቀበልኩኝ አስር ዓመታት አለፉ፡፡ እርሱ ወደ ራሱ ጠርቶኝ ከእርሱ ጋር ግላዊ ሕብረት እንዲኖረኝ ሰጠኝ፡፡ እስልምና ያንን ሊሰጠኝ አልቻለም ነበር፡፡


ጥዬአቸው ለመጣኋቸው ሙስሊም ወገኖቼ ጌታ ኢየሱስ ከእስልምና ጨለማ እንዲያወጣቸው በመጠየቅ ማልቀስን አቁሜ አላውቅም፡፡ የዚህን መጽሐፍ ገፆች በገለጣችሁ ቁጥር ይህ ጨለማ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ወደ መረዳት ትመጣላችሁ፡፡ በአላህ ስም ሁሉንም ዓይነት ክፋቶች የሚፈፅሙትን አሸባሪዎች የሚፈጥረው እስልምና ነው፡፡


አሁን መላው ዓለም እስልምና ምን እንደሚያስተምር ለመረዳት ይፈልጋል፡፡ በጣም ብዙ የሆነ የተሳሳተ መረጃ በመገናኛ ብዙኃን እና በኢንተርኔት ተሰራጭቷል፡፡ የእኔ ግብ እነዚህ ሰዎች እያደረጉ ያሉትን ነገር ለምን እንደሚያደርጉ መረዳት ትችሉ ዘንድ እናንተን መርዳት ነው፡፡


ነገር ግን ለቁጣ ላነሳሳችሁ አልሻም፡፡ እንድታምኑ ግን ላነሳሳችሁ እፈልጋለሁ - ለእስልምና ውድቀት እና በስሩ ላሉት ምርኮኞች በኢየሱስ ስም ነፃ መውጣት እንድታምኑ፡፡


የአዘጋጁ ማሳሰቢያ


በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ውስጥ አንድ አስገራሚ ጥቅስ ይገኛል ጥቅሱም “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል” ቁጥር 27. ከላይ ባነበብነው በምዕራፍ ሦስት ውስጥ የሆነው ነገር የዚህ ጥቅስ እውነተኛ ፍፃሜ ነው፡፡ ከተለያየ እምነት፣ ከተለያዩ ልምምዶች፣ የቆዳ ቀለም ዘርና ቋንቋ ውስጥ ያሉ ሰዎች የጌታ ኢየሱስን ድምፅ ሰዎች ሰምተዋል አሁንም ይሰማሉ፡፡ የእርሱን ድምፅ የሰሙትና የሚሰሙትም በተለያየ የእርሱ የራሱ መንገድ፣ እርሱ እራሱ ባዘጋጀው ጊዜና ቦታ እንዲሁም ሁኔታዎች ውስጥ ነው፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጆች እንደምናምነው በዚህም ገፅ አማካኝነት ብዙዎች የጌታ የኢየሱስን የጥሪ ድምፅ ሊሰሙና፣ ከእውተኛው የሰማይና የምድር ፈጣሪ አምላክ ጋር በመታረቅ የኃጢአትን ይቅርታ አግኝተው አዲስ ሕይወትን እንደሚያገኙና በአዲስ ሕይወትም እንደሚመሩ እናምናለን፡፡


በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ውስጥ እራሱ ጌታ ኢየሱስ ሲናገር እንደሚከተለው፡ “እኔ የበጎች በር ነኝ” በማለት የራሱን ሕዝቦች በእራሱ የሚመሩ የሚጠበቁ እና በሕይወት የሚኖሩ አድርጎ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ድምፁን ሰምተው እርሱን ለመከተል ከመጡ ነው፡፡ እርሱን የሚከተሉ ደግሞ ሃይማኖተኞች ብቻ አይሆኑም፣ እርሱን የመከተሉም ዓላማ ሃይማኖተኛ ማድረግ ሳይሆን ትክክለኛ የሕይወት ለውጥ ማግኘት ነው፡፡ ፍፃሜው ደግሞ የዘላለም ሕይወትን መቀበልና ለዘላለም በመንግስተ ሰማይ ውስጥ ከእርሱ ጋር መኖር ነው፡፡


እነዚህ ሁሉ አስደናቂ ነገሮች የሆኑት እግዚአብሔር የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ የሰውን ስጋ ለብሶ ወደ ምድር በገዛ ፈቃዱ በመምጣት ሕይወቱን ለኃጢአተኞች በመስቀል ላይ ሰጥቶ የኃጢአት ዕዳቸውን በመስቀል ላይ በመክፈሉ ነው፡፡


ይህ እውነት ክርስትናን የተለየ እምነት ከማድረጉ ውጪ ለሰዎች ልጆች ብቸኛ ተስፋም ጭምር አድርጎታል፡፡ አንባቢዎች ሆይ እናንተም እንደ እኛ የምትጋሩት የሰው ልጅነት፣ የሰው ችግር፣ የሰው ልጅ ሁሉ የኃጢአት ዕዳ፣ ከኃጢአትም የመነጨ ከፍተኛ ጥልቅ የሆነ ችግር አለባችሁ፡፡ ለዚህ ነው በየሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቁጥር 14-15 ውስጥ ጌታ ኢየሱስ፡ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፣ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል” በማለት ከተናገረ በኋላ አስደናቂውን የመስዋዕትነት ሞቱን የተናገረው፡ “ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ”፡፡


እዚህ ምዕራፍ ሁሉ ውስጥ በጎች ተብለው በምሳሌ አነጋገር የተጠቀሱት የእርሱ አማኞች ሊሆኑ በእርሱ የሚጠሩት ሰዎች ናቸው፡፡ ለእነርሱ ሁሉ እርሱ ነፍሱን በመስቀል ላይ ሰጥቶላቸዋል፣ መስዋዕት ሆኖ ሞቶላቸዋል፡፡ እነዚህን ወደ እርሱ መምጣት ያለባቸውን በጎቹን በፍቅሩና በአስደናቂው ቃሉ ውስጥ ባለው ድምፁ ይጠራቸዋል፣ እነርሱም ወደ እርሱ ይመጣሉ፣ የነፍስ እውነተኛ ሰላምና እርካታ የዘላለም ደስታና ተስፋንም ከእጁ ይቀበላሉ፡፡ ይህ ነው በግብፃዊው እስላማዊ ምሁርና ኢማም ሕይወት ውስጥ የሆነው፡፡ አንባቢዎች ሆይ! ዛሬ የክርስቶስን ጥሪ ለመስማት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ታውቃለህን? መልሱ አጭር ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ፈልጉና ማንበብ ጀምሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ድምፅ የሚሰማበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖት መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በግልፅ ለነፍሳችን ውስጥ የሚናገር መጽሐፍ ነው፣ አንብቡት ፈጣሪ በውስጡ ሲናገራችሁና ሲጠራችሁ ትሰማላችሁ፡፡ ድምፁን ከሰማችሁ በኋላ መውሰድ ያለባችሁ እርምጃ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ መጠየቅና በምህረቱ ይቅርታንና አዲስን ሕይወት መቀበል ነው፡፡ ከዚያም የሕይወት ለውጥ ታገኛላችሁ እናንተም ከተከታዮቹ አንዱ ትሆናላችሁ፣ እኛ የሆንነው እንደዚህ ነው፣ እኛን የረዳንና የጠራን ጌታ ድምፁን ያሰማችሁ ይጥራችሁም አሜን!!

 

ወደ ማውጫው መመለሻ

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ