የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሁለት

የሳቢያንና የአይሁዶች ሐሳቦችና ልማዶች ተፅዕኖዎች

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

1. የቃየልና የአቤል ታሪክ

ቁርአን እነዚህን ሁለት የአዳም ልጆች በስም አይጠቅሳቸውም ሆኖም ተንታኞች ቃቢልና ባቢል በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ ነገር ግን በምዕራፍ 5 ቁጥር 30-32 ላይ ስለእነሱ የሚከተለውን ተጽፎ እናገኛለን፡

‹ነፍሱም ወንድሙን መግደልን ለእርሱ ሸለመችለት ገደለውም ከከሳሪዎቹም ኾነ፣ የወንድሙንም ሬሳ እንዴት እንደሚሸሽግ ያሳየው ዘንድ አላህ መሬትን የሚጭር ቁራን ላከለት፣ ወይ እኔ የወንድሜን ሬሳ እሸሽግ ዘንድ እንደዚህ ቁራ ብጤ መኾን አቃተኝን? አለ ከጸጸተኞችም ኾነ፡፡ በዚህ ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ እነሆ ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላያ ያለማጥፋት ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕው እንዳደረገ ነው ማለትን ጻፍን መልክተኞቻችንም በግልጽ ተአምራት በእርግጥ መጡዋቸው ከዚያም ከዚህ በኋላ ከነሱ ብዙዎቹ በምድር ላይ ወሰንን አላፊዎች ናቸው፡፡›

በቃየልና በአቤል መካከል ውይይት ወይንም ደግሞ ጭቅጭቅ ተደርጎ እንደነበረ የ‹ዮናታን ታርገም› በሚባለው አፈታሪክ ጽሑፍ ላይና ‹በኢየሩሳሌም ታርገም› ላይ ተጠቅሷል፡፡ ቃየል እንደተናገረ የተነገረን ነገር ‹ለኃጢአት ምንም ቅጣት የለም እንዲሁም ደግሞ ለመልካም ምግባር ምንም ሽልማት የለም› በማለት ነው፡፡ ለዚህ መልስ እንዲሆን አቤል የመለሰው መልካም በእግዚአብሔር እንደሚሸለምና ክፉ ደግሞ እንደሚቀጣ ነው፡፡ በዚህ በመናደድ ቃየል ድንጋይን አነሳና ወንድሙን በዚያ በመምታት ገደለው፡፡ በዚህና በቁርአን ላይ በተጠቀሰው ትረካ መካከል ያለው ተመሳሳይነት አስደናቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን የቀረው የቁርአናዊ የአገዳደል አፈ ታሪክ ምንጭ ከፒርኪ ራቢ ኤልኤዘር ጋር ተዛማጅነት አለው የሱም አፈታሪክ መጽሐፍ ምዕራፍ 21 እንደሚከተው አቅርቦታል፡-

‹አዳም እና ረዳቱ በአቤል ላይ እያለቀሱና እያዘኑ ተቀምጠው ነበር፣ እንዲሁም በአቤልም በድን ላይ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው አላወቁም፡፡ ምክንያቱም በድን መቅበርን ከዚህ በፊት አይተው አያወቁም ነበርና፡፡ ከዚያም ከጓደኞቹ አንዱ የሞተበት ቁራ ወደእነርሱ መጣ፡፡ እርሱም የሞተውን ወስዶ መሬትን ቆፈረና እነሱ እያዩ በዓይናቸው ፊት ቀበረው፡፡ አዳምም አለ፡- ‹እኔም ልክ እንደ ቁራው አደርጋለሁኝ›፡፡ ወዲያውኑም ‹የአቤልን በድን ወስዶ መሬትን ቆፈረና ቀበረው›፡፡ ይህን አይሁዳዊ አፈ ታሪክ በቁርአን ላይ ከተሰጠው ጋር ስናወዳድረው የምናስተውለው ብቸኛ ልዩነት በዚህኛው ታሪክ አዳም የሞተውን አካል እንዴት መቅበር እንዳለበት ቁራው እንደተማረ ሲሆን በቁርአን ላይ ግን ከቁራው ትምህርትን የወሰደው ቃየል በመሆኑ ላይ ነው፡፡ በቁርአን ውስጥ ያለው ጽሑፍ ከአንድ ወይንም ከብዙ የአይሁድ መጽሐፍት ላይ ቃል በቃል የተተረጎመ አለመሆኑ ደግሞ ግልጥ ነው፡፡ ነገር ግን ልንገምት እንደምንችለው በቀደሙት የአረቢያ ታሪኮች ላይ  ስማቸው በተጠቀሱትና የመሐመድ ጓደኞች በሆኑት አንዳንድ አይሁዶች የተነገረው ታሪክ እንዳለ ተቀምጧል፡፡ ቁርአን በአዳም ምትክ ቃየልን ለመጥቀሱ ትክክለኛ የሚሆንን ምክንያትን ሊሰጠን የሚችለው ይህ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶችን በእነዚህ ንባቦች ሁሉ ውስጥ እናስተውላለን፡፡ እነዚህን ትናንሽ ልዩነቶች መሐመድ እራሱ በዓላማ ያደረጋቸው መሆኑ በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ እነዚህን አፈታሪኮች በቃላቸው የተማሯቸው አይሁዶች ከእርሱ ጋር ቢያያዙትም ስህተቱን የሰራው የአረቢያው ነቢይ ሳይሆን እነርሱ ናቸው፡፡ ይሄ በእርግጥ የትንሽ ወቅት ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ነጥብ ግን እዚህና በሌሎች ብዙ ሁኔታዎች ላይ መሐመድ ከቀደሙት የአይሁድ ጽሑፍ ምንጮች መጠቀሙን የመረጃ ፍንጮች ማግኘት መቻላችንን እርግጠኛ መሆኑን ነው፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ቁርአን በ32ኛው ቁጥር ላይ የተመዘገበው ከእርሱ በላይ ካለው አንቀፅ ጋር ምንም በቀጥታ የሚያይዘው ነገር ያለው አይመስልም፡፡ የሚያይዘው ነገር በእርግጥ ጠፍቷል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ‹ሚሽና ሳንሄድሪን› (ምዕራፍ 4 ቁጥር 5) ላይ ብንመጣ፣ እኛ ሁሉንም ነገር ሙሉ ለሙሉ ተመዝግቦ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህም ከዚህ በላይ ባለው ጥቅስና በአቤል አገዳደል መካከል ያለው ግንኙነት በጣም ግልጥ ይሆንልናል፡፡ ፔንታቱክ (የሙሴ አምስቱ መጽሐፍ) በሚነግረን ቃል ላይ አይሁዳዊው ተንታኝ ሲተነትን የሚነግረን እግዚአብሔር ከቃየል ጋር እንደተነጋገረ ነው፣ ‹ምን አደረግህ? የወንድምህ ደም ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል›፡፡ በአንቀፁ ውስጥ ደም የሚለው ቃል በብዙ ቁጥር ተጽፏል፣ ይህም በዕብራይስጥ ቋንቋ የሚያመለክተው በዓመፅ የፈሰሰውን ደም ነው፣ ስለዚህም ጸሐፊው የጻፈው፡ ‹ወንድሙን ስለገደለው ቃየል፣ እኛ ስለ እርሱ የተነገረውን ነገር አግኝተናል፣ ‹‹የወንድምህ ደሞች ድምፅ ይጮኻሉ›› እርሱም የተናገረው ‹የወንድምህ ደም› ሳይሆን ነገር ግን ‹የወንድምህ ደሞች› ነው፣ ይህም የእርሱ ደም እና የእርሱን ዘር ደሞች ነው፡፡ በዚህ ወቅት አዳም የተፈጠረው ብቻውን ነበር፣ በቅዱስ መጽሐፉ መሰረት ከእስራኤል ውስጥ አንዲት ነፍስን ያጠፋ ማንኛውም ሰው የሚቆጠረው ዓለሙን ሁሉ እንዳጠፋ ነው፡፡ እንዲሁም ማንም ሰው ከእስራኤል አንዲት ነፍስ ያዳነውን ሰው ደግሞ ቅዱስ መጽሐፍ የሚቆጥረው ዓለምን ሁሉ አድኖ እንደጠበቀ ነው፡፡› ስለዚህ የቅዱስ ቃል አተረጓጎም ትክክለኛነት ወይንም መሳሳት ብዙ አልተጨነቅንም፡፡ ይሁን እንጂ የቁርአን ምዕራፍ 5 ቁጥር 32 ቃል የዚህ ክፍል ቀጥታ ግልባጭ (ትርጉም) መሆኑን ማስተዋል በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

ስለሆነም በሚሽናህ የመጀመሪያው ክፍል ላይ ያለው ሐሳብ በቁርአን ላይ ተዘሏል፣ ለዚህም በቂ ምክንያት ሊሆን የሚችለው በመሐመድ ወይንም በነገረው ሰው ሙሉ ለሙሉ ግንዛቤን አላገኘም ነበር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሲጨመር ቁርአን 5 ቁጥር 32 እና ከዚያ በላይ ባሉት መካከል ያለው ግንኙነት ግልፅ ይሆናል፡፡

2. የአብርሃም ታሪክ

አብርሃምን ለማጥፋት ናምሩድ ካዘጋጀው እሳት የመዳኑ ታሪክ

ይህ የአብርሃም ታሪክ ትረካ በቁርአን ውስጥ በተከታታይ በአንድ ቦታ ላይ አይገኝም፣ ነገር ግን በተለያዩ የቁርአን ምዕራፎች ውስጥ በተቀነጫጨበ መልኩ ይገኛል፡፡ ስለዚህም መሐመዳውያን እነዚህን አንቀፆች መሰብሰብና ተከታታይ በሆነ አገናኝ አንቀፆች አያይዞ ማቅረብን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ይህም ‹‘Araisu'l Majalis or the Qisasu'l Anbiya› በሚባሉት መጽሐፍት እንደምናገኘው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አገናኝ ነገሮችም ከመሐመድ ልማዶች ውስጥ ነው የተጨመሩት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ሙስሊሞች ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ታሪክ ከአይሁዶች ሚድራሽ ራባ ተመሳሳይ ልማዳዊ ዘገባ ጋር ስናስተያየው በቁርአን ውስጥ ያለው የመሐመዳውያን ታሪክ ከአይሁዶቹ እንደመጣ ግልፅ ይሆናል፡፡ አንባቢ ይህንን ይመለከት ዘንድ በመሐመዳን ፀሐፊዎች የተጻፈውን ታሪክ በቅድሚያ እንተረጉመውና ከዚያም ወደ አጭሩና ቀላሉ የአይሁድ ልማዳዊዎች እንመጣለን፡፡ ከቁርአን ላይ ያሉት አንቀፆች ከቁርአን ትርጉም ላይ እንደሚከተለው ናቸው፡፡ ይህንንም ለማየት ከአብዱል ፊዳ በተውጣጣው ጽሑፍ እንጀምራለን፡-

‹አዛር የአብርሃም አባት›፣ እርሱ አለ፣ ‹ጣዖታትን ይሰራ ነበር፣ እርሱም አብርሃም እንዲሸጣቸው ይሰጠው ነበር፡፡ ነገር ግን አብርሃም ‹የሚጎዳውንና ምንም የማይጠቅመውን ነገር ማን ይገዛል?› በማለት ይናገር ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ሕዝቡን ወደ አንድ አምላክ አምልኮ እንዲመልስ ታላቁ እግዚአብሔር አብርሃምን ባዘዘው ጊዜ፤ አብርሃም አባቱን ጋበዘ፣ ይሁን እንጂ እርሱ ግብዣውን አልተቀበለም፡፡ ከዚያ ቀጥሎም ሕዝቡን ጋበዘ፡፡ ስለ አብርሃምም ያለው ይህ ነገር ይፋ በወጣና በዚያ አገር ንጉስ በነበረው በጉሽ ልጅ በናምሩድ ጆሮ በደረሰ ጊዜ ናምሩድ አብርሃምን (የእግዚአብሔርን ወዳጅ) ወሰደውና በትልቅ እሳት ውስጥ ጣለው፡፡ እሳቱም በረደና ምንም ችግር አላስከተለበትም፣ አብርሃምም ከእሳቱ ውስጥ ከጥቂናት ቀናት በኋላ ወጣ፡፡ ከዚያም ከሕዝቡ መካል አንዳንድ ሰዎች በእርሱ አመኑ፡፡›

እንግዲህ ያለን በጣም አጭሩ የአረብኛ ዘገባ ይህ ነው፡፡ ቀጥሎም እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነውንና በአራይሱል ማጃሊስ የተነገረውን ታሪክ ወደ መተርጎም እንተላለፋለን፡፡ ‹አብርሃምም ያለምንም እውነተኛው አምላክ እውቀት ወደ ዋሻው ዘንድ ተወሰደ፡፡ አንድ ምሽትም ወጣና የከዋክብትን ክብር አየ፣ እርሱም በጣም ተደንቆ እነሱን እንደ አምላኮቹ አድርጎ ሊቀበላቸው ወሰነ፡፡› ታሪኩም እንደሚከተለው ይቀጥላል፣ ይህም በቁርአን ውስጥ ይህንን በተመለከተ የተዘገቡትን በሙሉ በተቻለ መጠን በማስገባት፡- ‹ሌሊቱም በእርሱ ላይ በጨለመ ጊዜ ኮከብን አየ ይህ ጌታዬ ነው አለ፣ በጠለቀም ጊዜ ጠላቂዎች አልወድም አለ፡፡ ጨረቃንም ወጪ ኾኖ ባየ ጊዜ ይህ ጌታዬ ነው አለ፣ በገባም ጊዜ ጌታዬ (ቅኑን መንገድ) ባይመራኝ በእርግጥ ከተሳሳቱት ሕዝቦች እኾናለሁ አለ፡፡ ፀሐይንም ጮራዋን ዘርግታ ባየ ጊዜ ይህ ጌታዬ ነው ይህ በጣም ትልቅ ነው አለ፣ በገባችም ጊዜ ወገኖቼ ሆይ! እኔ ከምታጋሩት ሁሉ ንፁን ነኝ አለ፡፡ እኔ ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረው (አምላክ) ቀጥተኛ ስኾን ፊቴን አዞርኩ እኔም ከአጋሪዎቹ አይደለሁም አለ፡፡‹ ቁርአን 6.76-79፡፡ ‹እነርሱም የሚሉት የእርሱ አባት ጣዖታትን ይሰራ ነበር በማለት ነው፣ ሆኖም እራሱን ከአብርሃም ጋር ሲያዛምድ እርሱ ጣዖታትን መስራት እንደጀመረና አብርሃምንም እንዲሸጥ እንደሰጠው ነው፡፡ አብርሃምም (ሰላም በእርሱ ላይ ይሁንና) እነርሱን ይዞ በመውጣት እንደሚከተለው ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹የሚጎዳውንና ምንም የማይጠቅመውን ነገር የሚገዛ ማነው?› በማለት ጮኸ፡፡ ስለዚህም ማንም ሰው ከእርሱ ላይ አልገዛውም፡፡ ስለዚህም የማይሸጡ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ወንዝ ወሰዳቸው፡፡ እራሶቻቸውን መታቸውና እንደዚህ ‹‹የኔን መጥፎ ዋጋ ጠጡ› አላቸው፡፡ ይህንንም ያደረገው በሕዝቡና በውሸት ሃይማኖታቸውና ድንቁርና ላይ በማሾፍ ነው፡፡ ይህም የእርሱ ማሾፍና አመፀኝነት በሕዝቡ መካከልና በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ በጣም ገንኖ እስከሚታወቅ ድረስ ወጣ፡፡ ስለዚህም ሃይማኖቱን በተመለከተ ሕዝቡ ከእርሱ ጋር ተከራከሩ፡፡ ከዚያም እርሱ ለእነርሱ እንደሚከተለው ተናገራቸው ‹ወገኖቹም ተከራከሩት በአላህ (አንድነት) በእርግጥ የመራኝ ሲኾን ትከራከሩኛላችሁን? በእርሱም የምታጋሩት ነገር አልፈራም ግን ጌታዬ ነገርን ቢሻ (ያገኘኛል) ጌታዬም ነገሩን ሁሉ ዕውቀቱ ሰፋ አትገነዘቡምን? አላቸው፡፡ በናንተ ላይ በእርሱ ማስረጃን ያላወረደበትን እናንተ ማጋራታችሁን የማትፈሩ ስትኾኑ የምታጋሩትን (ጣዖታት) እንዴት እፈራለሁ! የምታውቁም ብትኾኑ ክፍሎች በጸጥታ ይበልጥ ተገቢው ማንኛው ነው? (አለ)፡፡ እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ እነዚያ ለነርሱ ጸጥታ አላቸው እሱም የተመሩ ናቸው ይኽችም ማስረጃችን ናት ለኢብራሁም በሕዝቦቹ ላይ (አስረጂ እንድትኾን) ሰጠናት የምንሻውን ሰው በደረጃዎች ከፍ እናደርጋለን ጌታህ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና፡፡› ቁርአን 6.80-83፡፡ እርሱም ድል እስኪያደደርጋቸውና እስከሚያሸንፈቸው ድረስ ነው፡፡ ከዚያም በእርግጥ አብርሃም አዛርን አባቱን እምነቱን እንዲቀበል ጋበዘው እርሱም ‹አባቴ ሆይ! እኔ ከዕውቀት ያልመጣልህ ነገር በእርግጥ መጥቶልኛልና ተከተለኝ ቀጥተኛውን መንገድ እመራሃለሁና፡፡› አለው ወ.ዘ.ተ፡፡ ከዚያም አባትየው ከልጁ ከአብርሃም ለቀረበለት ግብዣ ለመስማማት አልፈለገም፡፡ በዚያም ጊዜ አብርሃም ለሕዝቡ የእነሱን አምልኮ መካዱን ከፍ ባለ ድምፅ አወጀና የራሱን ሃይማኖት ገለጠ፡፡ እርሱም አለ፡- ‹ትግገዙት የነበራችሁትን አስተዋላችሁን? እናንተም የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁም (የተገዛችሁትን) እነሱም (ጣዖቶቹ) ለኔ ጠላቶች ናቸው ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር (እርሱ ወዳጄ ነው)፡፡›ቁርአን ምዕራፍ 26.75-77፡፡ እነርሱም መለሱ ‹አንተ ታዲያ ማንን ነው የምታመልከው?› አሉት፡፡  እርሱም ‹የዓለማትን ጌታ› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹ኒምሩድን ማለትህ ነውን?› አሉት ከዚያም እርሱ ‹አይደለም የፈጠረኝንና የመራኝን እርሱን ነው› አለ፡፡ ያም ጉዳይ በአምባ ገነኑ ገዢ በናምሩድ ጆሮ እስኪደርስ ድረስ ተስፋፋ፡፡ ከዚያም እርሱ ጠራውና እንዲህ አለው፡ ‹ኦ አብርሃም፣ የላከህን አምላክህን፣ ወደ እርሱ አምልኮ ሰዎችን የጋበዝካቸው እንዲሁም ከሌሎች ይልቅ የላቀ ኃይል ያለው ነው በማለት ያከበርከውን አላየኸውምን? እርሱ ምንድነው? ‹አብርሃምም አለ አምላኬ በሕይወት የሚያኖርና መግደል የሚችል ነው›፣ ኒምሩድም መለሰ፡ ‹እኔ በሕይወት አኖራለሁ እገድላለሁኝም›፡፡ አብርሃምም መለሰ፡ ‹አንዴት ነው አንተ በሕይወት የምታኖረው እና የምትገድለው?› እርሱም አለ፡ ‹እኔ በፍርድ ቤቴ ሞት የተፈረደባቸውን ሁለት ሰዎችን እወስዳሁ፤ አንደኛውንም እንዲሞት እገድለዋሁኝ፣ ስለዚህም እንዲሞት አደርገዋለሁኝ፣ ለሁለተኛው ደግሞ እምረውና እንዲሄድ አደርገዋለሁኝ ስለዚህም ሕይወቱን አኖርሁ ማለት ነው›፡፡ ከዚያም በኋላ አብርሃም ለእርሱ እንዲህ አለ ‹በእርግጥ እግዚአብሔር ፀሐይን ከምስራቅ ያመጣታል አንተ ከምዕራብ ልታመጣት ትችላለህን?› ያን ጊዜም ኒምሩድ ተደነቀና ምንም መልስን አልሰጠውም›፡፡

ታሪኩም ይቀጥላል አብርሃም የነበረበት ጎሳ በዓመት አንድ ጊዜ ታላቅ ክብረ በዓል የሚያደርጉበት ባህል እንደነበራቸው በመናገር ይቀጥላል በዚያም ጊዜ እያንዳንዱ ከከተማ ይወጣል፡፡ (ይህ ምናልባትም ከአይሁድ የዳስ በዓል ጋር የተምታታ ይሆናል ምክንያቱም በቁርአን ውስጥ ‹ፎርት› የሚለው ቃል ያለምንም ጥርጥር የጊዜው ቃል አይደለምና፣ መሐመዳውያን ስለ አባቶች እና ነቢያት በአጠቃላይ የሚግሩን ነገር በተመሳሳይ ባህርይ ሁኔታ የሚታወቅ ነውና)፡፡ ከተማውን ከመልቀቃቸው በፊት ነዋሪዎቹ አንዳንድ ምግቦችን ዝግጁ እንደሚያደርጉ ተነግሮናል፡፡ በመሆኑም በአምላኮቻቸው ፊት ያስቀምጡታል፣ እናም እንደዚህ ይላሉ፣ ‹የመመለሻችን ጊዜ ሲመጣ እንመለሳለን አምላኮችም ምግባችንን ይባርኩታል እኛም እንበላዋለን›፡ ስለዚህም በዚያን ጊዜ አብርሃም፣ ‹በዓለማትም ጌታ ሐሳባችሁ ምንድን ነው? (አለ)› ቁርአን 37.87፡፡ ጣዖቶቹንና በፊታቸው ያለውን ምግቡን አንስቶ እያሾፈባቸው እንዲህ አለ፣ ‹እኔ በሽተኛ ነኝም አለ፡፡ ከእርሱም የሸሹ ሆነው ሄዱ› ቁርአን 37.89-91፡፡ ከዚያም በእጁ በያዘው መጥረቢያ እነሱን መቆራረጥ ጀመረ ይህም ትልቁ ጣዖት ብቻ እስኪቀር ድረስ ሁሉንም ነው በእርሱም አንገት ላይ መጥረቢያውን አንጠለጠለውና ከዚያም እርሱ ወጣ፡፡ የከበረውና ከፍ ያለው ንግግርም ከዚህ እንደሚከተለው ነበር፡ ‹በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራ ማነው? እርሱ በእርግጥ ከበደለኞች ነው አሉ፡፡› ቁርአን 21.59፡፡ ስለዚህም ሰዎቹ ከበዓል አክብሮታቸው ወደ ጣዖቶቻቸው ቤት በተመለሱ ጊዜና ሁኔታውን ባዩ ጊዜ እንደዚህ አሉ ‹በአማልክቶቻችን ላይ ይህንን ያደረገው እርሱ ማነው? በእርግጥ እርሱ ፃድቅ ካልሆኑት አንዱ ነው፡፡ እነሱም አሉ ‹አብርሃም የሚባል ወጣት ስማቸውን ሲጠራ ሰምተነዋል› እርሱ ነው ይህንን ያደረገው፡፡ ከዚያም ያ ጉዳይ በአምባገነኑና በሕዝቡ ገዢ በኒምሩድ ጆሮ ዘንድ ደረሰ፡፡ እነርሱም አሉ በሰዎች ፊት አምጣው እርሱ ይህንን እንዳደረገ ይመሰክሩበት ዘንድ ‹እርሱንም ያለ ምስክር ሊይዙት አልወደዱም ስለዚህም ወደ ፊት ባመጡት ጊዜ ለእርሱ እንዲህ አሉት ‹ኦ አብርሃም በአማልክቶቻችን ላይ ይህንን አድርገሃልን?› አብርሃምም ‹በተቃራኒው መለሰና ከእነርሱ ትልቁ ነው ይህንን ያደረገው አለ›፡፡ እናንተ ከትናንሾቹ እኩል እርሱን በማምለካችሁ በጣም ተናዶ ነበር፡፡ ስለዚህም እርሱ ከሁሉም የበለጠና ትልቅ ስለነበር እነሱን ሁሉንም ሰባበራቸው፡፡ እናንተም የሚናገሩ ከሆነ እነሱን ጠይቋቸው› ነቢዩም እግዚአብሔር ይባርከው ይጠብቀውና  እንዲህ አለ ‹አብርሃም ሦስት ውሸቶችን ብቻ ተናገረ ሁሉንም ስለ ታላቁ አምላክ ሲል ነው የዋሸው፣ አንደኛው ‹እኔ ታምሜያለሁ ሲል›፣ ሁለተኛው ‹በተቃራኒው ከእነሱ ትልቁ ነው ይህንን ያደረገው ሲል› እናም ሦስተኛው ደግሞ ሳራን ለመውሰድ ንጉሱ ሲያቅድ ‹እርሷ እህቴ ናት ሲል› ነው፡፡

ስለዚህም አብርሃም ለእነሱ እንዲህ ሲላቸው፣ እነርሱ ወደራሳቸው ተመለሱ፣ እናም እንደዚህ አሉ፡ ‹በእርግጥ እናንተ ፃድቅ አይደላችሁም፡፡ እዚህ ነው እናንተ የምትጠይቁት ሰው እርሱ አደረገ የሚባለውን ያደረገባቸው አምላኮቻችሁ ደግሞ እነዚህ ናቸው ስለዚህም እነርሱን ጠይቋቸው› አብርሃምም የተናገረው ነገር ያንን ነበር፣ ‹እነሱ የሚናገሩ ከሆነ ጠይቋቸው› ስለዚህም የእርሱ ሰዎች እንዲህ አሉ፡ ‹እርሱ ካልተናገረ በቀር ልናገኝ የምችለው ነገር የለም› ከዚያም እንዲህ ተብሎ ነበር፡   ‹ኢብራሂም የሚባል ጎበዝ (በመጥፎ) ሲያነሳቸው ሰምተናል ተባባሉ ይመሰክሩበት ዘንድ በሰዎቹ ዓይን (ፊት) ላይ አምጡት አሉ፡፡ ኢብራሂም ሆይ! በኣማልክቶቻችን ይህንን የሠራህ አንተ ነህን? አሉት፡፡ አይደለም ይህ ትልቃቸው ሰራው ይናገሩም እንደ ኾነ ጠይቋቸው አለ ወደ ነፍሶቻቸውም ተመለሱ እናንተ (በመጠየቃችሁ) በዳዮቹ እናንተው ናችሁም ተባባሉ፡፡ ከዚያም በራሶቻቸው ላይ ተገለበጡ እነዚህ የሚናገሩ አለመኾናቸውን በእርግጥ ዐውቀሃል (አሉ)፡፡› ቁርአን 21.60-65፡፡ እናንተ ከትልቁ ጋር ትናንሾቹን ጣዖታት በማምለካችሁ፡፡ ከዚያም እርሱ ባቀረበው በዚህ ነገር ነገሩ ሁሉ በመደነቅ ተገለባበጠባቸው ከዚያም ጣዖታት እንደማይናገሩና በቀልንም እንደማይወስዱ አወቁ፡፡ ከዚያም እነርሱ እንደሚከተለው አሉ፡ ‹እነዚህ እንደማይናገሩ በእውነት አንተ ታውቃለህ› አብርሃም ያመጣው መከራከሪያም እንዳሸነፋቸው ባወቀ ጊዜ ለእነርሱ እንዲህ አላቸው ‹ምንም የማይጎዳችሁንና የማይጠቅማችሁን በእግዚአብሔር ምትክ ታመልካላችሁን? እናንተ በእግዚአብሔር ምትክ እነዚህን በማምለካችሁ ያሳፍራል እናንተ አሁን አልገባችሁምን?› ከዚያም ይህ ክርክር እነርሱን በረታቸው ጊዜ መልስም መስጠትን ባልቻሉ ጊዜ እነርሱ ያሉት ነገር የሚከተለው ‹ታዲያ ለእናንተ ምንም የማይጠቅማችሁንና የማይጎዳችሁን ነገር ከአላህ ሌላ ትግገዛላችሁን? አላቸው፡፡ ፎህ! ለእናንተ ከአላህ ሌላ ለምትግገዙትም ነገር አታውቁምን? (አለ)፡፡ ሠሪዎችም እንደ ኾናችሁ አቃጥሉት አማልክቶቻችሁንም እርዱ አሉ፡፡ (በእሳት ላይ ጣሉትም)፡፡ ቁርአን 21.66-68 ነበር፡፡ ይህንን በተመለከተ አብዱላ ኢብን ዑማር የተናገረው ‹አብርሃምን እንዲያቃጥሉት ያደፋፈራቸው ሰው ኩርዳዊ ነበር› ብሎ ሲሆን፤ ሹይቡል ጃባይ ያለው ደግሞ ‹ስሙ ዳይመን ይባል ነበር› ብሎ ነው፡፡ ከዚያም ታላቁ እግዚአብሔር ከዚያ ሰው እግር በታች ምድር እንድትሰነጠቅ አደረገና እርሱ ተዋጠ ይህም እስከ ትንሳዔ ቀን ድረስ ነው፡፡  ይህኛውም ያለምንም ጥርጥር የዘኁልቁ 16.31-34 ቅጂ ነው፡ ‹እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው። እነርሱም ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠ በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ። ምድሪቱ እንዳትውጠን ብለው በረሩ።› ከዚያም ኒምሩድና ሕዝቡ አብርሃምን ለማቃጠል ተሰብስበው እንዳለ እርሱን በአንድ ቤት ውስጥ ዘጉበትና እንደ በጎች ማጎሪያ የሆነ ግንብን ገነቡበት፡፡ ይህ ነው የእግዚአብሔር ቃል ‹አላቸው፡- የምትጠርቡትን ትግገዛላችሁን?› ቁርአን 37.95፡፡ ከዚያም እነርሱ በጣም ጠንካራዎችን እንጨቶችንና እጅግ ብዙ ዓይነት የሚነዱ ነገሮችን ሰበሰቡ፡፡ የምንጠቅሰው ጸሐፊ አብርሃም እንዴት ወደ እሳት እንደተጣለና ደህና ሆኖና ምንም ሳይሆን እንደወጣ ትረካውን ይቀጥላል፡፡ ታሪኩንም እንደሚከተለው ደመደመው፡ ‹በልማድ ላይ የተመዘገበው አብርሃም ተጠብቆ እንዲህ እንዳለ ነው፡፡

ስለዚህም እኛ አሁን ይህንን ታሪክ የአይሁዱ ሚድራሽ ራባ ከመዘገው ትረካ ጋር ለማወዳደር እናልፋለን፡ ይህም በሚድራሽ ራባ ምዕራፍ 17 ላይ ያለው የዘፍጥረት 15.7 ገለጣ ነው፡፡ ይህ አቀራረብ በሚዛን አልሃቅ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አረፍተ ነገሮችን ለመቃወም በሚዛኑ ማዎዚን ጥቅም ላይ ውሏል፡-

‹‹ታራ የጣዖታት ቀራጭ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እሱ ወደ ውጭ ወጥቶ በነበረ ጊዜ አብርሃምም በእርሱ ምትክ ሻጭ ሆኖ ተቀመጠ፡፡ አንድ ሰውም ጣዖታቱን ለመግዛት ፈልጎ መጥቶ በነበረ ጊዜ አብርሃም እንዲህ ይለው ነበር ‹ስንት ዓመትህ ነው?› እርሱም ሌላው ሰውየ ‹ሃምሳ› ወይንም ‹ስድሳ› ዓመቴ ነው ይለው ነበር፡፡ ከዚያም አብርሃም ለእርሱም እንዲህ ይለው ነበር፣ ‹የጥቂት ቀናት ዕድሜ ያለውን ነገር ለሚያመልክ ስድሳ ዓመት እድሜ ላለው ሰው ወዮለት› ይለው ነበር፡፡ ሌላውም ሰው አፍሮ መንገዱን ይሄድ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ አንዲት ሴት መጣች እርሷም በእጇ የስንዴ ዱቄት ያለበትን ሳህን ይዛ ነበር፡፡ ለእርሱም እንዲህ አለችው ‹ይኸውና ይህንን በእነሱ ፊት አኑረው!› እርሱም ብድግ ብሎ በትርን አንስቶ ሁሉንም ሰባበራቸው ከዚያም በትሩን ከእርሱ መካከል ትልቅ በሆነው እጅ ውስጥ አስቀመጠው፡፡ አባቱም ሲመጣ እንዲህ አለው ‹ማነው በእነርሱ ላይ ይህንን ያደረገው?› አብርሃምም ለአባቱ መለሰ፣ ‹ለአንተ ምን የተደበቀ ነገር አለ?› በእጇ የስንዴ ዱቄት ያለበትን ሳህን ይዛ አንዲት ሴት መጣችና እንዲህ አለችኝ ‹ይኸው ይህንን በፊታቸው አድርገው› እኔም በፊታቸው አስቀመጥኩት፡፡ ይኸኛውም አለ ‹እኔ በመጀመሪያ እበላለሁኝ› ያኛውም ‹እኔ ነኝ በመጀመሪያ የምበላው አለ›፡፡ ይኸኛው ከሁሉም ትልቁ ተነሳ በእጁም በትር ያዘና ሁሉንም ሰባበራቸው›፡፡ አባቱም ለእርሱ እንዲህ አለው፡ ‹አንተ ተረትን የምትነግረኝ ለምንድነው?› እነዚህ ያውቃሉን? አብርሃምም ለአባቱ መለሰ ‹ከንፈርህ የሚናገረውን ነገር ጆሮህ አይሰማውምን?› ታራም አባቱ ያዘውና ለኒምሩድ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ኒምሩድም ለአብርሃም እንዲህ አለው፡ ‹እኛ እሳትን እናምልክ› አብርሃምም ‹እሳትን የሚያጠፋውን ውሃን እናምልክ አለው›፡፡ ኒምሩድም ከዚያ ‹እኛ ውሃን እናምልክ› አለው፤ አብርሃምም መልሶ ‹ውሃን የሚያመጣውን ደመናን እናምልክ› አለው፡፡ ኒምሩድም ‹ደመናን እናምልክ› አለው ‹እንዲያ ከሆነ ደመናን ጠርጎ የሚወስደውን ነፋስን እናምልክ› አለው፡፡ ኒምሩድም ‹ነፋስን እናምልክ› አለው፡፡ አብርሃምም መለሰ ‹ነፋስን የሚቋቋመውን ሰውን እናምልክ› አለው፡፡ ኒምሩድም መለሰ ‹አንተ እንደዚህ ቃላትን ከእኔ ጋር የምትለዋወጥ ከሆነ ምንም ነገር አይሆንም፤ እኔ ከእሳት በስተቀር ሌላ ምንም ነገርን አላመልክም! እኔ ወደ እሳት መካከል እጥልሃለሁኝ የምታመልከው አምላክ መጥቶ ከዚያ ውስጥ ያውጣህ› አብርሃምም ወደ እቶን እሳቱ ውስጥ ተጣለ ከዚያም ዳነ››፡፡

ከዚህ በላይ እንደተቀመጠው የመሐመዳውያን ተረት በቀጥታ ከአይሁድ እንደተወሰደ በትክክል ግልጥ ነው፣ ሆኖም አንዳንድ ነገሮች በመሐመድ ግጥማዊ ግምቶች ተጨማምረዋል፡፡ እዚህም ላይ እንኳን መሐመድ ከአይሁዶች በአንደበት ሲተላለፍ የሰማውን ብቻ እንጂ ያነበበውን ታሪክ በትክክል አላስቀመጠውም፡፡ ታሪኩ በአዕምሮው ውስጥ የመቀመጡ ነገር ግልጥ የሚሆነው በትረካው ላይ እርሱ በመጨማመሩ ብቻ ሳይሆን በቁርአን ብዙ ክፍሎችም ውስጥ እንዲኖር ከማድረጉም ላይ ነው፡፡ በእርሱም ጊዜ ታሪኩ በአጠቃላይ ይዘቱ በጣም የታወቀ ስለነበር መሐመድ በየትኛውም ቦታ ላይ አጠቃላይ ሙሉ ትረካውን ማስቀመጥ ጠቃሚ መስሎ አልታየውም፡፡ በቁርአን ውስጥ ያሉት የመሐመድ ቃላት የሚያሳዩት ነገር ታሪኩ በእርሱ ተከታዮች ዘንድ በሚገባ የታወቀና ተቀባይነትም ያለው መሆኑን እርሱ የተገነዘበ መሆኑን ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ብዙ የአብርሃም ታሪኮች ሁሉ ይህም በመሐመድ ጊዜ በአረቢያ ይነገር እንደነበረ ነው፡፡

ከሚድራሽ ራባ ላይ ያለውን ጽሑፍ እዚህ ላይ ስንጠቅስ ዓላማችን መሐመድ ከዚያ ስራ ላይ ሰርቋል በማለት ለማረጋገጥ አይደለም፣ ነገር ግን ታሪኩ ሙሉ በሙሉና በዝርዝሩ ከዚያን በቀደሙት ጊዜያት በአይሁዶች ዘንድ የሚታወቅ የነበረ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህም አረቦቹ ስለዚህ የአብርሃም ታሪክ ያገኙት እውቀት ከዚህ ወይንም ከሌላ ተመሳሳይ ተረት ነው፡፡ ይህ ተረት በአንዳንድ መጽሐፎቻቸው ውስጥ መኖሩን አለመኖሩን ሊነግሩት የሚችሉትንና እና የእርሱ እምነት በእውነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲያረጋግጡለት የአይሁድ ጓደኞቹን ለማማከር መሐመድ ሄዶ መጠየቁ አጠራጣሪ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እኛ ያስተዋልነው ነገር በቁርአን ውስጥ የአብርሃም አባት በዘፍጥረት ላይ እንዳለው ታራ ሳይሆን አዛር ተብሎ መጠቀሱን ነው፡፡ ሆኖም ግን የምስራቅ አይሁዶች የአብርሃምን አባት አንዳንድ ጊዜ ዛራ በማለት ይጠሩት ነበር ይህም የአረባዊ ስያሜው የተበላሸበት ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይንም እንደገና መሐመድ ይህንን ስም ከሶርያ ምናልባትም ዩሲቢየስ አፃር በማለት ከተጠቀመበት ስያሜ ላይ ተምሮትም ሊሆን ይችላል፡፡ ዘመናዊ የፋርስ መሐመዳውያን ብዙውን ጊዜ ‹አዳር› በማለት ቢጽፉትም የሚሰጡት ድምፅ ግን በአረቦቹ ዘንድ እንዳለው አጠራር ‹ኣዛር› በማለት ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያው የፋርሳውያን አጠራር ‹አዳር› ሆኖ እያለ ሲሆን ዩሲቢየስ ከተጠቀመበት ጋር በጣም የሚጠጋጋ ነው፡፡ በፋርሶች ዘንድ ይህ ቃል ‹እሳት› ማለት ነው፣ ይህም በእሳት ላይ የሚኖር የመልአክ ስምና ስልጣን ነው ተብሎም ይታወቃል፣ የዖርማዝድ ጥሩ ፍጡራን ከሆኑትም አንዱ ነው፡፡ ይህ ነገር የአብርሃምን አባት ከ‹ኢዛድ› ወይንም እሳት ጋር በማዛመድ ለአብርሃም መልካምን ስም ለማስገኘት በማጂዎች ዘንድ ከተደረጉት አንዳንድ ሙከራዎች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎ ሊሆን ይችላል፣ እኛም የአብርሃምን በእሳት ውስጥ የመጣል አፈታሪክ ጅማሬ ለማወቅ እንችል ይሆናል፡፡ በጊዜው እንደሚገለጠው ሁሉ፤ እውነቱም የሚገኘው በአንዳንድ የአይሁድ ተንታኞች በተደረገ ቀላል ስህተት ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ በሙስሊሞች የሚወሰደውን የተለመደ የመከራከሪያ መንገድ ማሳየት መልካም ይሆናል፣ ይህም የዚህንና የሌሎችንም ተመሳሳይ የቁርአንን አፈታሪኮችን ምንጭ መገኘትና ቁርአን ከእግዚአብሔር ነው የመጣው የሚለውን ሐሳብ በትክክል የሚያፈርሰውን ለመቃወም የሚወስዱትን ክርክር ማሳየት ይጠቅማል፡፡ እነሱም ስለሃይማኖታቸው እውነታ ላቀረብነው ግልፅ ማስረጃ ለመመለስ ይገፋፋሉ፡፡ እነሱ የሚሉት ‹መሐመድ እነዚህን ታሪኮች ከአይሁዶች ያልተበደራቸው ቢሆንም፣ ነገር ግን በሌላ በኩሉ ከመልአኩ ገብርኤል በመገለጥ የተቀበላቸው ነው፣ ነገር ግን አይሁዶች የአብርሃም ዘር የሆኑት ይህንን ታሪክ ተቀብለውታል ይህም በራሳቸው የልማድ ስልጣን መሰረት ነው፣ ስለዚህም መታወቅ ያለበት የእነሱ ምስክርነት ቁርአን በጉዳዩ ላይ ለሚያቀርበው ትምህርት ታላቅ ምስክርነትን ሰጪ ነው› በማለት ነው፡፡

ለዚህም የሚረዳው በእንደዚህ ዓይነት ተረቶች ላይ እምነት የሚጥሉት ምንም የማያውቁ (ሃይማኖትን ያልተማሩ) አይሁዶች ብቻ ናቸው የሚለውን ማሳየት ነው፡፡ ምክንያቱም አዋቂዎቹ አይሁዶች ልማድ በሚባል በማናቸውም ነገር ላይ እምነት የላቸውምና፡፡ አብርሃምን በተመለከተ ብቸኛውና ተቀባይነት ያለው ማስረጃ የሚገኘው በአምስቱ የሙሴ መጽሐፍት ውስጥ ብቻ ነው ስለዚህም ይህ ህፃናዊ ወይንም የልጆች ተረት በቶራ ውስጥ በጭራሽ የሌለ መሆኑን መንገር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በተቃራኒውም ደግሞ ከዘፍጥረት ታሪክ ግልጥ እንደሆነው ሁሉ ኒምሩድ የኖረው ከአብርሃም ብዙ ትውልድ በፊት መሆኑ ግልጥ ነው፡፡ በቁራን ውስጥ ኒምሩድ በስም አለመጠቀሱ ግልጥ ቢሆንም ነገር ግን እንዳየነው ሁሉ ስሙ አለ፣ መሐመድ አብርሃም ወደ እሳት ውስጥ ተጥሏል በሚለው ተረት፣ በመሐመዳውያንም ልማድ ሆነ በቁርአን ተንታኞች ውስጥ እንደዚሁም ደግሞ በሚድራሽ ራባ ታሪክ ውስጥ አለ፡፡ እዚህ ላይ ከጊዜው ጋር የማይሄደው ነገር ታላቁ አሌክሳንደር የቱርኩን ሱልጣን ‹ኡትማንን› በእሳት ውስጥ ጣለው ብሎ አንድ ሰው እንደተናገረው ያህል ነው ይህም በመካከላቸው ማለትም በአሌክሳንደርና በኡትማን መካከል ያለውን እጅግ ረጅም ዘመን የማያውቅ ሰው ንግግር ብቻ ይሆናል፡፡ ይህም ኡትማን እንደዚህ ዓይነቱን ጀብዱ በፍፁም ሳያልፍበትና ሳያውቀው ማለት ነው፡፡

ከዚህም በላይ አብርሃም ከእሳት ውስጥ ምንም ሳይሆን ወጣ የሚለው ጠቅላላ ታሪክ የተመሰረተው በጥንታዊ የአይሁድ ተንታኝ የድንቁርና ስህተት ነው፡፡ ይህንንም ለመግለጥ እኛ የምናመለክተው የዮናታን ቤን ዑዘል ታርገምን ነው፡፡ ይህ ጸሐፊ የከለዳውያንን ዑር እንደ ቦታ ተጠቅሶ አግኝቶታል፡፡ ይህም አብርሃም በመጀመሪያ ከአገሩ ወደ ከነዓን ምድር እንዲወጣ ከእግዚአብሔር ጥሪን ሲቀበል የነበረበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ከተማ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሙካያር ተብሎ ይታወቃል፡፡ ዑር ወይንም ዑሩ የሚለውም ቃል በጥንት ባቢሎናውያን ከተማ ማለት ነው፡፡ ይህም በኢየሩሳሌምም ላይ እንደገና ተደግሟል (በአረብኛ ኡሩሻሎም የሚል ነውና) ‹የሰላም አምላክ ከተማ›፡፡ ነገር ግን ዮናታን ስለ ባቢሎን ምንም እውቀት አልነበረውም ስለዚህም ዑር የሚለው ቃል ከሂብሩው ዖር (ብርሃን) ጋር ተመሳሳይነት ትርጉም ያለው ቃል ነው በማለት ገመተ፣ ይህም ቃል በአርማይክ ቋንቋ ደግሞ እሳት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በዘፍጥረት 15 ቁጥር 7 ላይ የሚገኘውንና  ‹ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ አለው።› የሚለውን ቃል ‹ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ከእቶን እሳት ውስጥ ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ አለው።› በማለት አሳስቶ አስቀመጠው፡፡ እንዲሁም በዘፍጥረት 11.28 ላይ ያለውንም እንዲሁ እንደሚከተለው፡ ‹ኒምሩድ አብሃምን ወደ እቶን እሳት ውስጥ በጣለው ጊዜ ጣዖቶቹን ባለማምለኩ እሳቱ በእሱ ላይ ምንም ጉዳትን እንዳያመጣ ተደረገ› በማለት ጻፈው፡፡

ከዚህ እውነታና ማስረጃ የምንገነዘበው ነገር ጠቅላላ ታሪኩ የተነሳውና የተገነባው አንድ ጥቅስን በተሳሳተ መንገድ ከማብራራት ላይ ነው፡፡ ሆኖም ቅንጣትም የእውነታ መሠረት የለውም፡፡ ይህንን ስህተት በመስራት ዮናታን የመጀመሪያው ሰው ለመሆኑ አጠራጣሪ ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም ሐሳቡን ከሌሎች ተቀብሎትም ሊሆን ይችላልና፡፡ ከማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ብንመለከተው ውጤቱ ግን አንድ ነው፡፡

እንዳሳየነው ሁሉ ዮናታን ቤን ዑዘል እንደዚህ ዓይነት ስህተትን መስራቱ በጣም ማስደነቅ አይኖርበትም፡፡ የመለኮት መገለጥን አግኝቻለሁ ያለ ሰው ግን እንደዚህ ዓይነት ስህተትን እንደ እውነት አድርጎ መቀበሉና ማቅረቡ ግን በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እንዲሁም እኩል የሚገርመው ነገር በገብርኤል በኩል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብየዋለሁ በማለት በተናገረው መጽሐፉ ውስጥ በተለያዩ ብዙ ቦታዎች ላይ ከፋፍሎ ማስገባቱ እንዲሁም ተከታዮቹ እንዲያምኑት ማስተማሩም ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ በቁራንና በአይሁድ ቅዱስ መጽሐፍ መካከል ስላለው ተመሳሳይነት ይህንን (ይህ ታሪክ በስህተት ይገኛል ብሎ በመገመት) እና ሌሎችንም ጉዳዮች፣ መሐመድ፣ እርሱ ከእግዚአብሔር የተመደበ ነቢይ መሆኑን ማስረጃዎች ናቸው ብሎ ማለቱና ማቅረቡ በጣም ያስደንቃል፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

ከዚህ በላይ ያየነው ጽሑፍ በቅድሚያ ያነጣጠረው በአቤልና ቃየል ታሪክ ላይ ነው፡፡ በቁርአን ላይ ያለው የሁለቱ ወንድማማቾች ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው ጋር የማይሄድ ብቻ ሳይሆን ከፍጥረት ሕግጋትና ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ክቡርነት እውነታ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ በመሆኑም ቁርአንን አስቸጋሪ ደረጃና ጥያቄ ላይ ያስቀምጠዋል፡፡ በአጭሩም የቁርአን ምንጭ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እውነተኛው አምላክ አለመሆኑን ያለምንም ጥርጥር ያሳያል፡፡

በጣም ረጅም ዘገባና ማስረጃ የተሰጠው የአብርሃም ታሪክ ደግሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚናገረው የቁርአን ምንጩ ሰማይና ምድርን የፈጠረው እውነተኛው እግዚአብሔር ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡ 

እነዚህን ሁለት ማስረጃዎች በጥንቃቄና በማስተዋል የተመለከተ አንድ ሰው በርካታ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅና ለእነዚያም የሚሆኑ መልሶችን ለማግኘት አሁን መነሳት ይኖርበታል፡፡ ጥያቄዎቹም ያ ሰው የሚከተለው ሃይማኖት ትክክለኛ መሆን አለመሆኑን አውቆ በጣም ሳይዘገይ ትክክለኛውን የሕይወት መንገድ እንዲይዝ ይረዱታል፡፡

ማንኛውም ሃይማኖት በመጠኑም ቢሆን ስለ ዘላለም ሕይወት ይናገራል፡፡ ሆኖም የዘላለሙ ሕይወት ተስፋ እርግጠኛ የሚሆነው እምነቱ ትክክልና በእውነት ላይ ከተመሰረተ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጆችም ዋና ዓላማ ያንን እውነታ ለአንባቢዎች ማሳየት ነው፡፡ በተለይም ሙስሊም አንባቢዎች የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት እንዲችሉ ማግኘታቸውንም በእርግጥ ሊያውቁ የሚችሉበትን እውነት መጠቆም ነው፡፡ ይህም እውነት የሚገኘው አምላክ ሆኖ እያለ የሰውን ስጋ ለብሶ ወደዚህች ምድር በመጣው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር በመምጣት ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስና ፍፁም አምላክ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች ግን በኃጢአት ከእርሱ ደረጃ የወደቅንና ክብሩ የጎደለን ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርብን የሚችል አንድም በጎ ወይንም መልካም ነገር የለንም፡፡ ይህም የምንከተለውንም ሃይማኖታችንን ይጨምራል፡፡ የትኛውም ሃይማኖት አንድን ሰው በእግዚአብሔር ፈት ሊያቀርበው አይችልምና፡፡ 

ታዲያ መልሱ ምንድነው? እንዴት አድርገን ነው ከበደልነው ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን የምናገኘው? ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የሰውን ስጋ ለብሶ ለሰዎች ኃጢአት እራሱን አሳልፎ በሰጠው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መምጣት ነው፡፡ 

አንባቢዎች ሆይ! ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት ቀርባችሁ ኃጢአታችሁን በክርስቶስ በኩል ተናዛችሁ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን ብትጠይቁ እርሱ በክርስቶስ በጌታችን በኩል ይቅር በማለት ይቀበላችሁና፣ ይቅርም ይላችሁና አዲስን ሕይወት ይሰጣችኋል ይህ ነው የዘላለም ሕይወት፤ ካገኛችሁትና ከተሰጣችሁ በኋላም ከእናንተ አይወሰድም እርግጥ መሆኑንም እግዚአብሔር በሕይወታችሁ በሚሰራው ስራ ግልጥ ይሆንላችኋል፡፡ ከዚያም በጭፍን አትመላለሱም ከእግዚአብሔርም ጋር ትርጉም ያለውና እውነተኛ ህብረት ይኖራችኋል፡፡  የዚህ እውነተኛ ሕይወት ተካፋዮች እንድትሆኑ እግዚአብሔር በፀጋውና በምህረቱ ይርዳችሁ፤ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ