ቁርአን ተጠብቋልን?

Khaled

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

ቁርአን በምዕራፍ 15.9 ላይ የሚከተለውን ነገር ያቀርባል፡ ‹እኛ ቁርአንን እኛው አወረድነው እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን›፡፡

እንደ ኢብን-ካሊድ ባሉት በሙስሊም ተንታኞች መሠረት ይህ ማስታዎሻ የቁርአን ነው ምክንያቱም በዚያው ምዕራፍ ውስጥ ቀደም ብሎ የተሰጠ ሌላ ቁጥርን ማለትም 15.6 ‹አንተ ያ በርሱ ላይ ቁርአን የተወረደለት ሆይ! አንተ በእርግጥ ዕብድ ነህ አሉም› የሚለውን እናገኛለን፡፡ ሙስሊሞች የሚሉት በቁጥር 6 ላይ የተጠቀሰው ቃል ‹አንተ ያ በርሱ ላይ ቁርአን የተወረደለት ሆይ! ...› በማለት የሚናገረው ለመሐመድ ነው፡፡ ስለዚህም እዚህ ላይ የተጻፈው ማስታዎሻ ለቁርአን ለራሱ ነው የሚል አባባል አላቸው፡፡ ሙስሊሞች የሚደመድሙት ይህ የአላህ ቃል ኪዳን ነው ቁርአን ሊበከል (ማለትም ሊለወጥ) አይችልም እስከ አሁንም ድረስ እንደተጠበቀ በማለት ነው፡፡

አንዳንድ ክርስትያን አቃቤ እምነቶች ማስታዎሻ መሰረት (ቁርአን) የሚለውን የሚናገረው ለአላህ መልእክተኛ ነው በመጽሐፍ ቅዱስም ላይ የተገለጠውን ቃል ያጠቃልላል ይላሉ፡፡ ሙስሊሞች ብዙውን ጊዜ የሚናገሩት ግን ይህ ለቁርአን ብቻ የሚናገር ነገር ነው ምክንያቱም አላህ የጠበቀው ቁርአንን ብቻ ነው ይላሉና፡፡ ቁርአን ስለአይሁዶችና ስለክርስትያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ነገር ሁሉ በመውሰድ ቁርአን አይሁዶችና ክርስትያኖች የእግዚአብሔር እውነተኛና ያልተበረዘ መገለጥ አላቸው በማለት አንድ ሰው በጣም ግሩም የሆነን ክርክር ማድረግ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ሙስሊሞች ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሐሳቦች ስለማይቀበሏቸው የዚህ ጽሑፍ አላማ የእነሱ አቋም ወደ ብዙ ሎጂካዊ ችግሮች ውስጥ እንደሚመራቸው ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህም ለውይይት ያህል እኔ የምሄደው ሙስሊሞች በሚናገሩት ላይ ነው፡፡ ይህ ትርጉማቸው ከሌሎች ሙስሊማዊ እምነቶች ጋር አንድ ላይ ሲወሰድ ወዴት እንደሚያመራ ለማሳየት ነው፡፡

በሌሎች ቦታዎች ላይ ቁርአን ስለራሱ የሚናገረው ነገር ምንም ስህተት የሌለበት እንደሆነ ነው፡ ‹ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም ጥበበኛ ምስጉን ከኾነው ጌታ የተወረደ ነው፡፡› ቁርአን 41.42፡፡ እንዲሁም ደግሞ ‹ቁርአንን አያስተነትኑትምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡› ቁርአን 4.82፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ ሙስሊሞች የሚያምኑት በቁርአን ውስጥ ያተጠቀሱትና ያለፉት መገለጦች የተበላሹ ነበሩ የሚሉ ጥቅሶች እንዳሉ ነው ለምሳሌም ያህል፡-

‹አንተ መልእክተኛ ሆይ እነዚያ በክህደት የሚቻኮሉት ከነዚያ ልቦቻቸው ያላመኑ ሲኾኑ በአፎቻቸው አመንን ካሉትና ከነዚያም አይሁድ ከኾኑት ሲኾኑ አያሳዝኑህ እነርሱ ውሸትን አዳማጮች ናቸው፡፡ ...› ቁርአን 5.41፣ ‹ከእነሱም እርሱ ከመጽሐፉ ያይደለ ሲኾን ከመጽሐፉ መኾኑን እንድታስቡ በመጽሐፉ ምላሶቻቸውን የሚያጣምሙ ክፍሎች አልሉ፡፡ እርሱ ከአላህ ዘንድ ነውም ይላሉ፡፡ እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑም በአላህ ላይ ውሸትን ይናገራሉ› ቁርአን 3.78፣ ‹ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት ይህ ከአላህ ዘንድ ነው ለሚሉ ወዮላቸው ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት (ኃጢአት) ወዮላቸው› ቁርአን 2.79፣ ‹ከነዚያም ይሁዳውያን ከኾኑት ሰዎች ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አልሉ፣ ...› ቁርአን 4.46፣ እና ‹ቃል ኪዳናቸውን በማፍረሳቸው ረገምናቸው ልቦቻቸውንም ደረቆች አደረግን ...› ቁርአን 5.13፡፡

ይሁን እንጂ በሌላ ጎኑ ደግሞ አሁንም ቁርአን ሙስሊሞችን የሚያዛቸው ነገር ባለፉት መገለጦች እንዲያምኑ ነው፡- ‹ለነዚያም ወደ አንተ በተወረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው የሚያምኑ በመጨረሻይቱም (ዓለም) እነርሱ የሚያረጋግጡ ለኾኑት (መሪ ነው)› ቁርአን 2.4፡፡ ‹መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ ምእመኖቹም (እንደዚሁ) ሁሉም በአላህ በመላእክቱም በመጽሐፍቱም በመልእክተኞቹም ከመልክተኞቹ በአንድም መካከል አንለይም (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ ሰማን ታዘዝንም ጌታችን ሆይ ምሕረትህን (እንሻለን) መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው አሉም› 2.285፡፡ ‹በአላህ አመንን በኛ ላይ በተወረደውም (በቁርአን) በኢብራሂምና በኢስማኤልም በኢስሓቅም በያዕቆብም በነገዶችም ላይ በተወረደው ለሙሳና ለዒሳም ለነቢያትም ሁሉ ከጌታቸው በተሰጠው (አመንን) ከነርሱ መካከል አንድንም አንለይም እኛ ለርሱ ታዛዦች ነን በል› ቁርአን 3.84፡፡

እነዚህም የበፊት መገለጦች የሚከተለውን የሚጨምሩ ናቸው፡- ‹እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን እነዚያ ትእዛዝን የተቀበሉት ነቢያት በነዚያ ይሁዳውያን በኾኑት ላይ በርሷ ይፈርዳሉ ሊቃውንቱና ዐዋቂዎቹም ከአላህ መጽሐፍ እንዲጠብቁ በተደረጉትና በርሱም ላይ መስካሪዎች በኾኑት (ይፈርዳሉ) ሰዎችንም አትፍሩ ፍሩኝም በአንቀፆቹም አነስተኛን ዋጋ አትለውጡ አላህም ባወረደው ሰው እነዚያ ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው› ቁርአን 5.44፣ ‹ምድርንም መልካሞቹ ባሮቼ ይወርሷታል፣ ማለትን ከመጽሐፉ (ከተጠበቀው ሰሌዳ) በኋላ በመጽሐፎቹ በእርግጥ ጽፈናል› ቁርአን 21.105፡፡ ‹በፈለጎቻቸውም (በነቢያቶቹ ፈለግ) ላይ የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲኾን አስከተልን ኢንጂልንም በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሣጭ ሲኾን ሰጠነው› ቁርአን 5.46፡፡

ከዚህ በላይ እስከ አሁን ያየናቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው እንከልሳቸው፡-

1.   ቁርአን ተጠብቋል

2.   ከቁርአን በፊት የነበሩት የእግዚአብሔር መገለጦች ቶራን መዝሙርንና ወንጌልን ይጨምራል፡፡ እነዚህም መጽሐፍት የመጽሐፍ ቅዱስን ብዙውን ክፍል የሚሰጡት ናቸው፡፡

3.   ቁርአን ቶራ መዝሙርና ወንጌል ሁሉም የአላህ ቃላት ናቸው፡፡

4.   የእግዚአብሔር ቃል አይለወጥም፡፡

5.   ከቁርአን በፊት የመጣው መገለጥ ተበክሏል (ተቀይሯል)፡፡

6.   ሙስሊሞች እነዚህ የበፊት መጽሐፍት እውነተኞች ከእግዚአብሔር የመጡ መገለጦች ናቸው በማለት ቢቀበሉም፣ እንደ መጨረሻ መገለጥና ብቸኛ የተጠበቀ አድርገው ማመን ያለባቸው ቁርአንን ብቻ ነው፡፡

አሁን እንግዲህ ከዚህ በላይ ያየናቸውን እውነታዎች ከዚህ በታች ካለው ሎጂክ ጋር ለመመልከት የሚከተሉትን ነጥቦች ማየት ይኖርብናል፡-

ሀ. ቁርአን  ቶራ መዝሙርና ወንጌል ሁሉም የአላህ ቃል ናቸው

ለ. በአሁኑ ጊዜ ያለው ቶራ መዝሙርና ወንጌል የተበከሉ ናቸው

ሐ. የአላህ የመጨረሻው ቃል ቁርአን ግን ተጠብቋል፡፡

ስለዚህም የሚከተሉት መደምደሚያዎች ላይ ለመምጣት እንችላለን እነዚህም፡-

አንደኛ መደምደሚያ፡- የአላህ አንዳንድ ቃላት ተበክለዋል፡፡

ሁለተኛ መደምደሚያ፡- አንዳንድ የአላህ ቃላት ሳይበከሉ ተጠብቀዋል፡፡

ከዚህ በላይ ባሉት ሎጂካዊ መደምደሚያዎች ላይ በመመስረት የሚከተሉትን ቅደም ተከተል ያላቸውን መነጋገሪያ ሐሳቦች ማዋቀር እንችላለን፡-

ዋነኛው ሐሳብ፡- አንዳንዶቹ የአላህ ቃላት የተበከሉ ናቸው፡፡

አነስተኛው ሐሳብ፡- ቁርአን የአላህ ቃል ነው፡፡

መደምደሚያ ሐሳበ፡- ቁርአን የተበላሸ ሊሆን ይችላል፡፡

ወይንም ደግሞ ከዚህ በላይ ያለውን በሚከተለው ሌላ መንገድ ልናስቀምጠው እንችላለን፡፡

ዋነኛው ሐሳብ፡- አንዳንዶቹ የአላህ ቃላት የተጠበቁ ናቸው፡፡

አነስተኛው ሐሳብ፡- ቶራ መዝሙራትና ወንጌል የአላህ ቃላት ናቸው፡፡

መደምደሚያ ሐሳብ፡- ቶራ መዝሙራትና ወንጌል የተጠበቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ዋናው ችግር

አላህ የቀደሙትን መገለጦቹን በደካማ ሰዎች እንዲበላሹ ስለፈቀደ ይህ ደግሞ ስለ አላህ ሊኖረን ወደሚችለው ከዚህ ወደሚከተለው አንድ ግምተ-ሐሳብ (ወይንም መላምት) ይመራናል፡-

1.   አላህ ደካማ አምላክ ነው፡- የቀደመውን የራሱን መገለጥ መጠበቅ አልቻለም፡፡ እርሱም ጊዜ በሄደ ቁጥር ብዙ ኃይልና ስልጣንን ያገኛል፣ ምክንያቱም አሁን የተገመተው እርሱ መጠበቅ የቻለው የመጨረሻውን መገለጥ ቁርአንን ብቻ ነውና፡፡

2.   አላህ ለሰዎች ግድ የለውም፡- አላህ በተመሳሳይ መገለጦች ሰዎች ሲሳሳቱ ምንም ግድ የሌለው አምላክ ነው፡፡ እንደገና ደግሞ ምንም እንኳን መልእክቱ እንዲበላሽ አላህ መፍቀዱን ሰዎች ወደ መገንዘብ ባይመጡም፣ የተሳሳተ መልክትን በመከተላቸው ግለሰቦችን በገሃነም እሳት ውስጥ አሁንም ይቀጣል፡፡ በመሆኑም አላህ ፍትሃዊ አይደለም ማለት ነው፡፡

ከዚህ በላይ ባሉት ሃሳቦች መሠረት እነዚህ ሦስት መገለጦች (ማለትም ቶራ፣ መዝሙራትና ወንጌል) የተበላሹ ከሆነ ቁርአን ላለመበላሸቱ እንዴት ልናምንና በእርሱስ ላይ እንዴት ልንታመን እንችላለን? አላህ የመጨረሻውን መገለጥ ቁርአንን ለመጠበቅ ችሏል በማለት አንድ ሰው እንዴት ሊታመን ይችላል? ይህም ደካማ የሆኑ ሰዎች የመጀመሪያውን የአላህ መገለጥ እንደፈለጉ ሲያደርጉት ደካማ ሆኖ ፈቅዶላቸው እያለ ማለት ነው፡፡

ወይንም ደግሞ ምናልባትም አላህ አምስተኛ መገለጥን ፈልጎ ቢሆንስ? ምናልባትም ይህንን አምስተኛ መጽሐፍ ልኮም ሊሆን ይችላል ያም ደግሞ በባሃ-ዑላ የተሰጠው መገለጥና በባሃኢ እምነት መስራች ይሆንን?

 ‹የእግዚአብሔር ቃላት አይለወጡም› የሚሉት ሙስሊሞች ይህንን የያዙትን አቋማቸውን ከዚህ በላይ ከተነሱት ሎጂካዊ እውነታዎች ጋር በጣም ጠቃሚና አሳማኝ በሆነ ሁኔታ የሚያስታርቁት እንዴት ነው?

 ሙስሊሞች ሁሉ እዚህ ላይ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባችኋል እናም ከዚህ በታች ካሉት አማራጮች አንዱን መምረጥ አለባችሁ፡-

 1.   ቁርአን የተጠበቀ ነው (አልተበላሸም) የቀደሙት መገለጦች ግን ተበላሽተዋል፡፡ ቁርአንን ለመጠበቁና የቀደሙት መገለጦችን እንዲበላሹ አላህ በማድረጉ ሊኖር የሚችለው መግለጫ ይህ ብቻ ነው እርሱም፤ አላህ ደካማና ፍትሃዊ አይደለም ማለት ነው፡፡

2.   ቁርአንም ልክ እንደሌሎቹ መገለጦች ተበላሽቷል (ተለውጧል)፡፡ ስለዚህም ሌሎች የተበከሉ መገለጦችን ሙስሊሞች ስለማያነቡ ቁርአንንም ማንበብ አይኖርባቸውም፣ ወይንም ይህንን የተበላሸውን ቁርአንን እንዲነበብ ሙስሊሞች እንደሚያስገድዱት ሁሉ እነዚያንም የተበከሉ መገለጦች በግድ ማንበብ ይኖርባቸዋል፡፡ 

3.   ቁርአን ተጠብቋል ሌሎችም የቀደሙት መገለጦች እንደዚሁ ተጠብቀዋል፡፡ ስለዚህም እነዚያን ታማኝ የእግዚአብሔር መገለጦች፤ መጽሐፍ ቅዱስን ሙስሊሞች የግድ ማንበብ ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡

4.   ቁርአን የተበላሸ ነው ነገር ግን የቀደሙት መገለጦች የተጠበቁ ናቸው፡፡ በእርግጥ ቁርአንን መተውና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አለባቸው ማለት ነው፡፡

አንድ ሰከንድ እንደገና ታገሱኝ እኔ ገና አልጨረስኩም፡-

ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ሙስሊሞች ሦስተኛውን ምርጫ ካነሱ፣ ሌላ ችግር ያጋጥማቸዋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ቁርአን የቀደሙትን መገለጦች እጅግ በጣም ብዙ በሆኑ ቦታዎች ላይ ይቃረናቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቁርአን ሊታይ የሚችለው የውሸት መልእክት ብቻ ሆኖ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም ማለት ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የስህተት ምንጭ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የቀደመውን መገለጦቹን ሊቃወም የሚችልን መገለጥ በፍፁም ሊሰጥ አይችልም፡፡

እነዚህን አማራጮች ሙስሊሞች የማይወዷቸው ከሆነ ግን ሌላ አማራጭ ሊነግሩን ይገባቸዋል እባካችሁ አማራጮችን ንገሩን!

ከዚህ በላይ ባለው ባቀረብኩት አጠቃላይ ምልከታና ድምዳሜ ላይ ምን የተሳሳተ ነገርን አይታችኋል?

የእኔን መሠረታዊ ነጥቦች ካልተቀበላችኋቸው ከዚያም መደምደሚያዎቼንም አትቀበሏቸው ነገር ግን የሚከተለውን እንድታደርጉልኝ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡-

ቁርአን ተጠብቆ የቆየ መሆኑን አረጋግጡልኝ፡፡ ይህንንም ማድረግ ያለባችሁ ሎጂካል በሆነ መንገድ ነው፡፡ ይህም መሆን ያለበት ቁርአንን ባለመድገም ነው ምክንያቱም እነዚያን ቃላት መድገም መደጋገም ብቻ የሚሆን ነውና፡፡ ይህም ማስረጃ ሊሆን አይችልም ወይንም የቀደሙት መገለጦችን ተበላሽተዋል በማለት ጥረት ማድረግ ቁርአን የተበላሸ ላለመሆኑ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልምና ወይንም ቁርአን ሳይንሳዊ ተዓምራት አሉት (እኔ ውሸቶች ናቸው ብዬ የምላቸውን) ብሎ ማቅረብም ትክክል አይደለምና፡፡ ከዚህ በላይ የቀረቡትን ፍልስፍናዊ አቀራረቦች እንድትመልሱልኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡

ስለዚህም ሎጂካል በሆነ መንገድ እና ለአስተሳሰብ ተቀባይነት ባለው መንገድ ሙስሊሞች የሚናገሩት ቁርአን ፍፁም ተጠብቋልና የቀደሙት የእግዚአብሔር መገለጦች ተበለሽተዋል የሚለው አባባል ለእግዚአብሔር ፍትህና ታላቅ ኃይል ስድብ ላለመሆኑ አሳዩኝ፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ከዚህ በላይ ያየነው ሎጂካዊ አቀራረብ ለሙስሊሞች ትልቅ ጥሪን ያቀርባል፡፡ ይህም ጥሪ አንደኛ ሙስሞሊች ሁሉ በተከፈተ አዕምሮ ቁርአንን እንዲመረምሩትና መልእክቱን እንዲያስቡበት፤ ሁለተኛ በቁርአን ውስጥ የቀደሙ መገለጦች የተባሉትን ቶራን፣ መዝሙራትንና ወንጌልን ምን እንደሆኑ በማንበብ እንዲመረምሩና በመልክቶቻቸውም ላይ እንዲያስቡባቸው ይጣራል፡፡

የዚህ ድረ ገፅ አዘጋጆች ይህንን አስፈላጊ ሎጂካዊ አቀራረብ የምርና ወሳኝ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ የሃይማኖት መሰረታዊ ስጦታ ከዘላለም ሕይወት ጋር የተያያዘ በመሆኑ እውነታ ላይ ሙስሊሞች ሁሉ እንደሚስማሙ እንገምታለን፡፡ የዘላለም ሕይወት ተስፋና እውነታ ደግሞ መመስረት ያለበት በእውነት ላይ መሆን ይገባዋል፡፡ የተጠቀሱትን ሦስት መጽሐፍት የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጠው ወጥ የሆነ መልእክት አስደናቂ ነው፡፡ የሰው ዘር በሙሉ በራሱ ውስጥ ምንም መልካምነት እንደሌለውና በምድር በሚሰራው ስራ በኩል እግዚአብሔር ሊቀበለው እንደማይችል በግልጥ ይናገራል፡፡

ከእውነተኛው ፈጣሪ ከእግዚአብሔር የራቀውንና የሲዖል ፍርድ የሚገባውን ሰው እግዚአብሔር ሊቀበለው የሚችለው እንዴት ነው? ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ነው መልሱም እጅግ በጣም ግልጥ በሆነ መንገድ ከማስረጃ ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀርቧል፡፡ ቸሩና በፍርዱ ፍፁም ስህተት የሌለበት እግዚአብሔር መንገዱን የከፈተው የሰውን ስጋ ለብሶ በመጣው በልጁ በጌታ ኢየሱስ የመስዋዕትነት ሞት በኩል ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በከፈለው ዋጋ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ ስለ እርሱ ይቅር ብሎ ሊቀበላቸው ቃል እንደገባ ለማየት የምትችሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው፡፡፡ በመሆኑም ለዘላለም የሚጠቅማችሁን መልእክት የያዘውን መጽሐፍ አግኝታችሁ እንድታነቡ፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በሚያስተላልፉ ቤተክርስትያናት ውስጥ የሚሰጠውን መልእክት እየሄዳችሁ እንድትሰሙ ጥሪያችንን በክርስቶስ ፍቅር እናስተላልፍላችኋለን፡፡ እግዚአብሔር ወደ ልጁ መንግስት በፀጋው ይጥራችሁ፡፡

 

የትርጉም ምንጭ:Is the Quran Preserved?

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ